ECMA Gold

ECMA / ኢካገባ

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለዩናይትድ ካፒታል ፋይናንሻል ሰርቪስ ኃ.የተ.የግ.ማህበር የኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ ሰጠ

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን (ባለስልጣኑ) የናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል ግሩፕ ተቀጥላ ኩባንያ (Subsidiary) ለሆነው ዩናይትድ ካፒታል ፋይናንሻል ሰርቪስስ ኃ.የተ.የግ.ማህበር የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት ፈቃድ ሰጥቷል።

ይህም ተቋሙን በኢትዮጵያ ውስጥ ተቀጥላ ኩባንያ በማቋቋም እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ የተሰጠው የመጀመሪያው የውጭ ኢንቨስትመንት ባንክ ያደርገዋል። የተሰጠው ፈቃድ ድርጅቱ በኢንቨስትመንት ባንክ ዘርፍ ስር እንዲሠራ የሚፈቅድ ሲሆን፤ ባለስልጣኑ ከዚህ በተጨማሪ የአምስት (5) የቦርድ ዳይሬክተሮችን ሹመት ያጸደቀ ከመሆኑም በላይ ለአራት (4) ተሿሚ እንደራሴዎችም ፈቃድ ሰጥቷል።

አርብ ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተሰጠው ይህ ፈቃድ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የተፈቀደላቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎችን ጠቅላላ ቁጥር ወደ አስራ ስምንት (18)፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ባንኮችን ቁጥር ወደ ሰባት (7) ከፍ አድርጎታል። ይህም የሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ተግባራዊነት እና ልማት እያሳየ ያለውን ተጨባጭና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ያሳያል።

በይፋዊው የፈቃድ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ እንደገለጹት፣ እንደ ዩናይትድ ካፒታል ያለ የፓን-አፍሪካዊ ተቋም ወደ ገበያው መግባቱ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ዕድገት ላይ ታሪካዊ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጸው፤ ሁነቱ እያደገ ባለው የሀገሪቱ የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ተዓማኒነት እና እየተከናወኑ ባሉ የማሻሻያ እርምጃዎች ላይ ጠንካራ እምነት መኖሩን እንደሚያሳይ አመልክተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፣ እንዲህ ያሉ ዕድገቶች ለኢትዮጵያ የገበያ አቅም እና ለታየው ተቋማዊ መሻሻል የተሰጡ ትልቅ እውቅናዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የገበያውን ጥልቀት፣ አቅም እና ቀጣናዊ ውህደት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ አመልክተዋል። በተመሳሳይም ፈቃድ የተሰጣቸው አገልግሎት ሰጪዎች ከፍተኛ የገበያ ሥነ-ምግባርን፣ የኮርፖሬት አስተዳደር መርሆዎችን እና የቁጥጥር ማዕቀፎችን ማክበር እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተው አሳስበዋል::