በእሱፈቃድ ተረፈ
በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመቋቋም ላይ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ወይም የካፒታል ገበያ ሲባል በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ለመሆኑ የካፒታል ገበያና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ማለት ምን ማለት ነው? ለአገራችን ያለው ፋይዳስ ምንድነው? የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ወይም የካፒታል ገበያ ተዋናዮች እነማን ናቸው? የሚሉትን ጨምሮ አንዳንድ ተያያዥ ጉዳዮችን እያነሳን ለማየት እንሞክራለን፡፡
- የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ምንነት?
የሰነደ ሙዓለ ንዋይ (Securities) ማለት በገንዘብ ሊተመን የሚችል ባለቤትነትን የሚገልጽ ሰነድ ማለት ሲሆን ሊሸጥ፣ ሊለወጥ ወይም በዋስትና ሊሰጥ የሚችል መብት የሚያቋቁም ሰነድ ነው፡፡ በእኛ አገር የሚታወቁት የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ዓይነቶች አክሲዮን፣ ቦንድና የግምጃ ቤት ሰነድ ናቸው፡፡ ባደጉት አገሮች የተለያዩ ዓይነት የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ይገበያያሉ፡፡ እነዚህም አክሲዮኖችን (Shares)፣ የዕዳ ሰነዶችን (Debt Instruments)፣ ብድሮችን (Loans)፣ ቦንዶችንና ሌሎች ወደ ኩባንያ ካፒታልነት ሊቀየሩ የሚችሉ ስምምነቶችን ያካትታል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም በመንግሥት ወይም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የወጡና ለግብይት የሚውሉ የሕዝብ የብድር ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን፣ ለወደፊት የሚፈጸሙ የውል ዓይነቶችን (Futures)፣ ያለ ግዴታ የመግዛት ወይም የመሸጥ መብት ለገዥው የሚሰጡ ሰነዶችን (Options)፣ ተዛማጅን (Derivatives) እና በጋራ የኢንቨስትመንት ፈንድ ውስጥ ያለ የድርሻ ክፍልፋይ (Units in a Collective Investment Scheme) ይይዛል፡፡
እነዚህንና ሌሎች የካፒታል ገበያ ሰነዶችን በአገራችን በተማከለ ገበያ ለማገበያየት እንዲያመች እንደ ሌሎቹ አገሮች የራሱ የሆነ ሒደትን መዘርጋት፣ መደገፍ፣ መቆጣጠር ብሎም መከታተል የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የካፒታል ገበያ አዋጅ ወጥቶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2021 አንቀጽ 2(62) መሠረት ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ማለት ከላይ በሌሎች አገሮች ግብይት ይደረግባቸዋል የተባሉትን ሰነዶች ጨምሮ፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ናቸው ብሎ የሚወስናቸውን ማናቸውም በግብይት የድርሻ ባለቤትነትን የሚያረጋግጡና በባለሥልጣኑ ፈቃድ መሠረት የሚተላለፉ ሰነዶችን ይጨምራል፡፡
የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ደግሞ እነዚህ ሰነዶች የሚገበያዩበትና ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ የተሰጠው የግብይት መድረክ ወይም ሥርዓት ነው፡፡ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ፣ ባደጉት አገሮች ከሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ከፍተኛ ድርሻ ከመያዝ ባለፈ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ደረጃ የመወሰን አቅም አለው፡፡
- በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ታሪካዊ ዳራ
አገራችን ለውጭ ሥልጣኔ ቅርብ ብትሆንም ለረጅም ዓመታት የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሳይኖራት ቆይታለች፡፡ ታሪካዊ ዳራውን ስንመለከት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እ.ኤ.አ. በ1897 የኢትዮ ጂቡቲን ምድር ባቡር ሐዲድ ለመዘርጋት የ40 ሚሊዮን ፍራንክ አክሲዮን በፈረንሣይ አገር መሸጣቸውን ታሪክ መዝግቧል፡፡ በእሳቸው ዘመን የተቋቋመው የመጀመርያው ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ ሲመሠረት አክሲዮኖቹ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ኒውዮርክ፣ ፓሪስ፣ ለንደንና ቪየና እንደተሸጡ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ1956 የኢትዮጵያ የቄራዎች ድርጅት ለሕዝብ ሽያጭ የወጣ ሲሆን፣ እሱን ተከትሎ እ.ኤ.አ. ከ1957 እስከ 1963 ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ጠርሙስ ፋብሪካ (Ethiopian Bottling Company)፣ ኢንዶ-ኢትዮጵያን ጨርቃ ጨርቅ፣ ኤችቪኤ ኢትዮጵያ፣ ሳባ ጠጅ፣ ተንዳሆ ተክልና የአዲስ አበባ ባንክ ለሕዝብ ሽያጭ መውጣታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪ እ.ኤ.አ. በ1959 ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ለሕዝብ ሽያጭ የቀረበ ድርጅት መሆኑንና በወቅቱ በሦስት ወራት ውስጥ ከአክሲዮን ሽያጭ 2.5 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ ኤችቪኤ የተባለው የሆላንድ ኩባንያ አብዛኛውን አክሲዮን መግዛቱ ይነገራል፡፡ እንዲሁም ሕዝቡም ቀላል ሊባል በማይችል መልኩ በግብይት መሳተፉንና ድርሻ መግዛቱን ጄዲቮን ፒስኬ የተባለ ጸሐፊ፣ «አክሲዮንና የአክሲዮን ግብይት በአዲስ አበባ» በሚለው መጽሐፉ ከትቦት ይገኛል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1960 ዓ.ም. በኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ (State Bank of Ethiopia) ውስጥ የአክሲዮን ግብይት መምርያ መቋቋሙ የአክሲዮን ግብይቱን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህንን መምርያ ማደራጀት የአክሲዮን ገበያን ለማስፋፋት በመንግሥት የተወሰደ የመጀመርያው ተቋማዊ አደረጃጀት ዕርምጃ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ የተለያዩ ኢንቨስተሮችን በግብይት በማሳተፍና ዋጋ እንዲሰጡ በማድረግ፣ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ዋጋ እንዲወሰን ይደረግ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1965 የአክሲዮን ግብይት እያደገ በመሄዱ፣ የሕዝብን እምነት በማግኘቱ፣ ኢኮኖሚውም ዕድገት በማሳየቱ፣ አዳዲስ የሚፈጠሩ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የአክሲዮን ድለላ ሥራ ውስጥ በመግባታቸው በወቅቱ ገበያው አድጎ ነበረ ለማለት ያስደፍራል፡፡
ታዲያ እ.ኤ.አ. ከ1959 እስከ 1963 ለሕዝብ ሽያጭ ከወጡ ድርጅቶች በተደረገው የአክሲዮን ግብይት፣ በአጠቃላይ 61 ሚሊዮን ብር የተጠጋ ሽያጭ ሲፈጸም ኤችቪኤ የተባለው የኔዘርላንድስ ኩባንያ 41 ሚሊዮን ብር ማለትም 67 በመቶ በተጠቀሱት ድርጅቶች አክሲዮን ድርሻ የገዛ መሆኑን አቶ አርዓያ ደበሳይና አቶ ታዴዎስ ሐረገወርቅ፣ «የካፒታል ገበያ ዕድገት በኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሔት ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በመምርያ ደረጃ ሲመራ የነበረው የአክሲዮን ግብይት ሥራ በ1963 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሥረቱን ተከትሎ፣ እ.ኤ.አ. በ1965 የአዲስ አበባ የአክሲዮን ንግድ ማኅበር (Addis Ababa Share Dealing Group) በሚል ተደራጅቶ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህ ማኀበር በብሔራዊ ባንክ በኩል የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገለት ሰባት በሚሆኑ ድርጅቶች መካከል የአክሲዮንና የቦንድ ግብይት ሲያደርግ ነበር፡፡ እነዚህ ሰባት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የአዲስ አበባ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ሳቢያን ዩቲሊቲ ኮርፖሬሽንና አልፍሬድ አቤል የሚባሉ ግለሰብ እንደነበሩ በታሪክ መዛግብት ተከትቦ ይገኛል፡፡
የአክሲዮንና የቦንድ ግብይቱ በእነዚህ ድርጅቶች መካከል ከመካሄዱ በተጨማሪ ድርጅቶቹ ለደንበኞቻቸውም ግዥ/ሽያጭ ይፈጽሙ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማኅበሩ ከላይ በመግቢያው የተዘረዘሩ ድርጅቶችን ጨምሮ አሥራ አምስት የሚሆኑ ኩባንያዎችን መዝግቦ (Listing) አክሲዮኖቻቸውንና የመንግሥት ቦንዶችን ያገበያይ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ግብይቱ በግልጽ ጨረታ የሚከናወን እንደነበረ፣ ዋጋ በማኅበሩ አባላት ኮሚቴዎች በየሳምንቱ እየተወሰነ የሚፈጸም መሆኑን፣ የግብይት ዓይነቱም ወዲያውኑ የሚፈጸም ግብይት (Spot Trade)፣ ወደፊት የሚፈጸም ግብይት (Forward Trade) እና ያለግዴታ የመግዛት ወይም የመሸጥ መብት ለገዥው የሚሰጥ ሰነድ ግብይት (Options Trade) እንደነበሩ ታውቋል፡፡ ከታሪክ መዛግብት ለመረዳት እንደሚቻለው ሁሉም የማኅበሩ አባል ድርጅቶች አክሲዮኖቻቸውን ለሕዝብ የመሸጥ ሥራ በተሳካ መልኩ ያከናወኑ ሲሆን፣ ሕዝቡ ስለአክሲዮን ግብይት ዕውቀት ከማግኘት ባለፈ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንደነበረ ታውቋል፡፡ በዚህ ሒደት በ1960 የንግድ ሕግ መውጣቱ ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ ሚና የተጫወተ ቢሆንም፣ በ1975 ማኀበሩ በሽግግር ጊዜ በደርግ መንግሥት እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተማከለ የካፒታል ገበያ ለማቋቋም ያልተሳኩ ሙከራዎች ቢደረጉም፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁርጠኝነት በማሳየትና የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ረገድ መንግሥት ብዙ ርቀት ተጉዞ እነሆ የተማከለ የካፒታል ገበያ በአገራችን ሊጀመር ጥቂት ጊዜያት ቀርቶታል፡፡
- የካፒታል ገበያ ፋይዳ
የካፒታል ገበያ፣ ኩባንያዎች የረጅም ጊዜ የገንዘብ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የአክሲዮን ወይም የዕዳ ሰነድ የሚያወጡበት አሠራር ነው፡፡ እነዚህ ሰነዶች በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (Securities Exchange) ወይም ባልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያ (Over-the-Counter Market) የሚገበያዩበት አሠራር በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ቁጥጥርና ድጋፍ እየተደረገለት የሚካሄድ በመሆኑ፣ አሠራሩን በመመርያ በመደንገግ ግብይት የሚደረግበት የኤሌክትሮኒክ መሠረተ ልማት ተዘርግቷል፡፡
በእኛ አገር የሚታወቀው በምሥረታ ላይ ያለ ማንኛውም የአክሲዮን ማኀበር አክሲዮኖቹን ለሕዝብ ለመሸጥ ሲፈልግ፣ በንግድ ሕጉ መሠረት በአደራጆች ወይም በመሥራቾች አስተባባሪነት ሽያጭ በመፈጸም ድርጅቱን ለማቋቋም የሚያበቃ ገንዘብ ለመሰብሰብ ይሞክራል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ግብይቶች የሚካሄዱበት የገበያ ደረጃ ባደጉት አገሮች የመጀመሪያ ደረጃ ገበያ (Primary Market) እና የሁለተኛ ደረጃ ገበያ (Secondary Market) ተብሎ ለሁለት ይከፈላል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ገበያ የሚካሄደው ግብይት የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጪዎች በውክልና ሻጮች (Investment Bank/Underwriter) በኩል ድርሻ ለሕዝብ የሚሸጡበት ገበያ ነው፡፡ በዚህ ገበያ አክሲዮኖች፣ ቦንዶችና ሌሎች በገንዘብ ሊተመኑ የሚችሉ ሰነዶች ለመጀመሪያ ጊዜ በማውጣት (Intial Public Offering) እና በመሸጥ አዲስ ካፒታል የሚሰበስቡበት ገበያ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ በምሥረታ ላይ የሚገኝ አክሲዮን ማኀበር አክሲዮኖቹን ለሕዝብ ሲሸጥ፣ ካፒታሉን ለማሳደግ የወሰነ አክሲዮን ማኀበር አክሲዮኖቹን ለገበያ ሲያቀርብ፣ እንዲሁም አክሲዮን ማኀበር ወይም የመንግሥት የልማት ድርጅት የዕዳ ሰነድ ለሽያጭ ሲያቀርብ ግብይቶቹ በመጀመሪያ ደረጃ ገበያ ይካሄዳሉ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ገበያ የተደረገው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ደላላዎች አማካይነት በባለቤትነት ከያዘው ሰው ወደ ሕዝብ የሚሸጥበት መድረክ የሁለተኛ ደረጃ ገበያ ይባላል፡፡ በእኛ አገር በመጀመሪያም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ የሚከናወነው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይት የተማከለ ካለመሆኑ ባሻገር፣ በሁለተኛ ደረጃ ግብይት ትክክለኛውን የሰነዶች ዋጋ ማወቅ የሚቻልበት አግባብ የለም፡፡ ይህም ግብይቱ ግልጽነት እንዳይኖረው ከማድረጉም በላይ፣ የአክሲዮን ማኀበራትን ሀብት በትክክል ከማወቅና ዘርፉ ለአገር ዕድገት ሊያበረክት ከሚችለው አስተዋጽኦ አንፃር አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም በዘርፉ ሀብታቸውን ያፈሰሱና ገንዘባቸውን በከንቱ የተበሉ እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም እውነታ ዘርፉ የሕግ ማዕቀፍ ተበጅቶለት ቁጥጥርና ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ሁነኛ አመልካች ነው፡፡ በሁለቱም ደረጃ ገበያዎች በአገራችን የተቋቋመ ተቆጣጣሪ ተቋምና የተማከለ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ባለመኖሩ፣ ግብይቱና ሒደቱ በተደራጀና ቁጥጥር በሚደረግበት መልኩ እየተከናወኑ ባለመሆኑ የዘርፉ ዕድገት የተገደበ መሆኑ ተስተውሏል፡፡ ይህም ከዚህ በፊት ባልተማከለ መንገድ የሚደረገውን የአክሲዮን ግብይት ሕግ፣ ሥርዓትና ቁጥጥር ወደ የሚደረግበት ግብይት በማምጣት አገርም ሆነ የገበያ ተዋንያን ከዘርፉ የሚያገኙትን ጥቅም ያሳድጋል ተብሎ ይታመናል፡፡
አክሲዮን ማኀበራት በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ገበያ ላይ በመሳተፍ አክሲዮን/ቦንድ በመሸጥ የሚፈልጉትን ገንዘብ ሊሰበስቡ የሚችሉ ሲሆን ሕዝቡም አክሲዮን በመግዛት፣ ባለቤትነት ድርሻ ከእነ ጥቅሙ እና/ወይም ወለድ የማግኘትና በሚፈልገው ጊዜ መልሶ መሸጥ የሚችልበት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፡፡ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አዲስ ያረቀቀው «የሕዝብ ሽያጭ አቅርቦትና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይት መመርያ (Draft Directive on the Public Offering and Trading of Securities)» ተግባራዊ የሚሆነው በሕዝብ ኩባንያዎችና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ይሆናል፡፡ ለዚህ ዓላማ ሲባል የሕዝብ ኩባንያ ማለት ከሃምሳ (50) በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ሆኖ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ለሕዝብ ለሽያጭ የሚያወጣ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም አክሲዮን ማኀበር በመጀመሪያ ደረጃም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ገበያ ለመሳተፍ የሚችለው ከሃምሳ (50) በላይ ባለአክሲዮኖች ሲኖሩት፣ ከዚህ በተጨማሪ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ (Prospectus) አውጥቶ በባለሥልጣኑ ሲያፀድቅ መሆኑን መመርያው ይደነግጋል፡፡ የደንበኛ ሳቢ መግለጫው ስለአክሲዮን ማኀበሩ አጠቃላይ ዓላማ፣ ገንዘቡ እንዴት ሊሰበሰብ እንደታለመ፣ ከተሰበሰበ በኋላ እንዴት ሥራ ላይ እንደሚውል፣ የኩባንያውን የኦዲት ሪፖርትና ያለፉት ዓመታትን ትርፍ ማካተት አለበት፡፡ እንዲሁም የደንበኛ ሳቢ መግለጫው አጠቃላይ የማኀበሩን ታሪክና የወደፊት ዕቅድ የሚያሳይ፣ ማኀበሩ የፍርድ ቤት ክርክር ወይም ውሳኔ ካለበት እሱን የሚገልጽ ሆኖ በባለሥልጣኑ መፅደቅ ይጠበቅበታል፡፡ ማስታወቂያ ማስነገርና ይዘቱ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ አካል እንደ መሆናቸው፣ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ሳይፀድቅ አክሲዮን ማኀበሩ ማንኛውንም የአክሲዮን ሽያጭን የተመለከተ ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙኃን ማስነገር እንደማይቻል በመመርያው ተመላክቷል፡፡
በአንፃሩ የአክሲዮን ማኀበር ሆኖ የዕዳ ሰነድ ሊያወጣ ከፈለገ የሕዝብ ኩባንያ ከመሆን በተጨማሪ፣ ብድር የመመለስ አቅሙ ፈቃድ ባለው ብድር የመመለስ ብቃት ምዘና አገልግሎት በሚሰጥ ድርጅት (Credit Rating Agency) ተመዝኖ የዕዳ ሰነድ ሊያወጣ ይችላል፡፡ ማንኛውም ከአክሲዮን ማኀበር ውጭ ያለ የንግድ ማኀበር ዓይነት የሕዝብ ኩባንያ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ የማያሟላ በመሆኑ፣ አክሲዮንም ሆነ ቦንድ ወይም የሚተላለፉ የግዴታ ሰነዶችን ማውጣት እንደማይችል በንግድ ሕጉ አንቀጽ 180 ተመላክቷል፡፡ ባለሥልጣኑ አክሲዮን ማኀበራት ሆነው የባለአክሲዮኖቻቸው ቁጥር ከሃምሳ በማነሱ ምክንያት የሕዝብ ኩባንያ መሥፈርት ማሟላት የማይችሉ ድርጅቶችን ለመደገፍ የሚረዳ መመርያ የማውጣት ሥልጣን በአዋጅ ተሰጥቶታል፡፡
የካፒታል ገበያ በዋናነት አክሲዮን ማኀበራት የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን በማውጣትና በመሸጥ ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ካፒታል በመሰብሰብ ድርጅታቸውን ማስፋፋት የሚችሉበትን ዕድል ይዞ መጥቷል፡፡ ሌላው የካፒታል ገበያ ፋይዳ መንግሥት የዕዳ ሰነዶችን በማውጣትና በመሸጥ ከዚህ በፊት ከሌሎች አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚገኝ ብድር የሚሠሩትን ትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመሥራት ያስችለዋል፡፡ በተጨማሪ መንግሥት የልማት ድርጅቶቹን ድርሻ በካፒታል ገበያ በኩል ለሕዝብ በመሸጥ ከዚህ በፊት በብድር የሚሠሩ አገራዊ ፕሮጀክቶችን በመደጎም ሥራ ላይ በማዋል የሚፈጠረውን የካፒታል አቅም ክፍተት ሊሞላ ይችላል፡፡ ይህንን በማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት በመፍጠር በአገር ደረጃ በገቢ በሚሰበሰበውና በአጠቃላይ ወጪ (Expenditure) መካከል ያለውን ልዩነት ሊያጠብ/ሊያስተካክል ይችላል፡፡ ሕዝቡም ከዚህ ድርሻ በመግዛት የባለቤትነት ወይም የትርፍ ክፍፍልና ሌሎች ጥቅሞችን ያገኛል፡፡
በቀጣይ የካፒታል ገበያ ተቆጣጣሪና ተዋናዮች እነማን ናቸው? ሚናቸውስ ምንድነው? የሚሉትን ይዤ እስከምቀርብ ቸር እንሰንብት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሕግ አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው bterefe@ecma.gov.et ማግኘት ይቻላል፡፡