የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ባለፈው የበጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገም እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ፈቃድ ከተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ባንኮች እና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አከናዋዮች ጋር በዛሬው ዕለት የጋራ ውይይት ያደረገ ሲሆን በውይይቱም የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ተገኝቷል፡፡
በውይይቱ ባለፈው የበጀት አመት በፈቃድ አሰጣጥ፣ በቁጥጥር እና የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ አፈፃፀም ላይ ባለስልጣኑ ያከናወናቸው ተግባራት አና ዋና ዋና ስኬቶች የቀረቡ ሲሆን ስኬቶችን በማስቀጠል እና ችግሮችን በጋራ በመፍታት የካፒታል ገበያውን የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዉይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ ከካፒታል ገበያው ተሳታፊዎች ጋር ቋሚ የሆነ ውይይቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው መሰል ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹ ሲሆን ንቁ፣ ግልጽ እና ጠንካራ የካፒታል ገበያ ለመገንባት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ከካፒታል ገበያ ተስታፊዎች ጋር የሚካሄደው አመታዊ ውይይት በነገው ዕለትም ፈቃድ ከተሰጣቸው የሰነደ-ሙአለ ንዋይ አማካሪዎች ጋር የሚቀጥል ሲሆን፣ ይህም አገራዊ የካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳሩን ለማሳደግ የሚደረጉ ውይይቶችና ትብብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማሳያ ነው፡፡