አክስዮኖቻችሁን ማስመዝገብ ሲገባችሁ ላላስመዘገባችሁ አክስዮን ማህበራት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ እና ለህብረተሰቡ የተሰጠ ማሳሰቢያ
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የካፒታል ገበያውን ለመቆጣጠር በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 አንቀጽ 3 መሰረት የተቋቋመ ተቋም ሲሆን ባለስልጣኑ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ አንዱም የሰነደ ሙአለ ንዋዮች ምዝገባ ነው፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1248/2013 አንቀጽ 75 መሰረት ማንኛውም ለህዝብ የሚሸጥ ሰነደ ሙአለ ንዋይ ለሽያጭ ወይም ለገበያ ከመቅረቡ በፊት በባለስልጣኑ መመዝገብ እንዳለበት የሚደነግግ በአዋጁ እና በመመሪያው ከምዝገባ ነጻ የተደረጉ ካልሆኑ በስተቀር በባለስልጣኑ ያልተመዘገቡ ሰነደ ሙአለ ንዋዮችን ለገበያ ማውጣትም በአዋጁ አንቀጽ 106 (5) መሰረት በወንጀል የሚያስቀጣ ተግባር ነው፡፡
ሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጪዎችም አዲስ የሚወጡ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችም ሆነ ከዚህ ቀደም ወጥተው በሰነደ ሙአለ ንዋይ ባለቤቶች የተያዙ ሰነደ ሙአለ ንዋዮችን የመመዝገብ ግዴታ የተጣለባችው ሲሆን አስቀድመው በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ባለቤቶች የተያዙ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን የማስመዝገቢያ ቀነ ገደቡም ህዳር 16 ቀን 2018 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡
ስለሆነም ከዚህ ቀን በኋላ ያልተመዘገቡ ሰነደ ሙአለ ንዋዮችን ለግብይት ማቅረብ እና መገበያየት በካፒታል ገበያ አዋጁ ከ7 እስከ 15 አመት ጽኑ እስራት እንዲሁም ከ150,000 እስከ 300,000 በሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣ የወንጀል ተግባር በመሆኑ አክስዮኖቻቸሁን ያላስመዘገባችሁ አክስዮን ማህበራት ምንም አይነት ከአዲስም ሆነ ነባር አክስዮኖች ሽያጭ እና ግብይት ጋር የተያያዘ እንቅስቃሴ እንዳታከናውኑ፣ እንዳታስተዋወቁ እና አክስዮን የሚያገበያዩ ቢሮዎች ያሏችሁ ኩባንያዎችም የማገበያየት ስራ እንዲያቆሙ እንድታደርጉ በጥብቅ እያሳሰብን ይህንን በማታደረጉ አክስዮን ማህበራት ላይም ሽያጮቹ የሚሰረዙ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከገንዘብ ቅጣት ባለፈም የስራ ሃላፊዎችን እና የቦርድ አባላትን እስከማገድ እና በጥቁር መዝገብ እንዲሰፍሩ እስከማድረግ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ የምንወስድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የወንጀል ሀላፊነትንም በተመለከተ ከተገቢው የፍትህ አካላት ጋርም በትብብር የምንሰራ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ህብረተሰቡም ይህንን ተገንዝቦ መመዝገብ ሲገባቸው ያልተመዘገቡ አክስዮኖችን እንዳይገበያይ እና አክስዮኖችን ከመገበያየቱ በፊት መመዝገባቸውን አሊያም ከምዝገባ ነጻ የተደረጉ መሆናቸውን እንዲያረጋግጥ፣ እንዲሁም በባለስልጣኑ ፈቃድ ባልተሰጣቸው ደላሎች እና አሻሻጭች አማካኝነት እና ፈቃድ ከተሰጠው ሰነደ ሙአለ ንዋይ ገበያ ወይም ያልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያ ውጭ አክስዮኖችን እንዳይገበያይ በጥብቅ እያሳሰብን አክስዮናቸውን ማስመዝገብ ሲገባቸው ሳያስመዘግቡ የቀሩ አክስዮን ማህበራትን እና ሳያስመዘግቡ የአዲስም ሆነ ነባር አክስዮኖችን ግብይት ማከናወን የቀጠሉ አክስዮን ማህበራት እንዲሁም ፈቃድ ያልተሰጣቸው ደላላ እና አሻሻጮች ሲገጥሙ ጥቆማ ለመስጠት አሊያም ስለጉዳዩ መረጃ ለመጠየቅ ከዚህ በታች የተገለጸውን አድራሻ መጠቀም የሚቻል መሆኑን እንገልጻለን፡፡
አድራሻ : አዲስ አበባ ቦሌ መንገድ ከፍላሚንጎ ሬስቶራንት በስተጀርባ ምናየ ህንፃ
ስልክ: +251 011557 8250 | +251 011557 8310
ድረገፅ፡ ecma.gov.et
ኢሜይል፡ Securities@ecma.gov.et
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን
ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም