ECMA Gold

ECMA / ኢካገባ

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለሁለት አዲስ ኢንቨስትመንት ባንኮች ፈቃድ ሰጠ

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከሰፊ የፈቃድ ማመልከቻ ግምገማ ሂደት በኋላ ለኤ ኤም ጂ ኢንቨስትመንት ባንክ ኃላ/የተ/የግ/ማ እና ለ ናይልብሪጅ ኢንቨስትመንት ባንክ ኃላ/የተ/የግ/ማ የኢንቨስትመንት ባንክነት ፈቃድ መስጠቱን በደስታ ይገልጻል።

በተጨማሪም ባለስልጣኑ የሁለቱን አዳዲስ ኢንቨስትመንት ባንኮች ስምንት (8) ተሿሚ እንደራሴዎች እና የአሥር (10) ቦርድ አባላት ሹመትን አጽድቋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ዳግማዊት ሽፈራው ፈቃዱን ህዳር 4 ቀን 2019 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና መስሪያ ቤት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ለሁለቱ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ባንክ አመራሮች በይፋ ያስረከቡ ሲሆን፤ በባለስልጣኑ ፈቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች ጠቅላላ ቁጥር ወደ ሀያ ሦስት (23) ከፍ ሲል፤ የኢንቨስትመንት ባንኮች ቁጥር ወደ አስራ አንድ (11) ከፍ ብሏል።

በፈቃድ አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ላይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ዳግማዊት ሽፈራው በዕለቱ ፈቃድ ለተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ባንኮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ኢንቨስትመንት ባንኮቹ ደረጃውን የጠበቀ ሙያዊ አገልግሎት በመስጠት በገበያው ላይ ግልጽ እና ፍትሀዊ ግብይት እንዲሰፍን እንዲሁም ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በኢትዮጵያ ጠንካራ እና አካታች የካፒታል ገበያ ስርዓት እንዲገነባ ያለውን ቁርጠኝነት እየገለጸ ኤ ኤም ጂ ኢንቨስትመንት ባንክን እና ናይልብሪጅ ኢንቨስትመንት ባንክን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል።