የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የዕቅድ አፈጻጸም ምልከታ እና አጠቃላይ የተቋማዊ ዝግጁነት ሁኔታን ለመገምገም ያለመ የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።
ምልከታው ባለሥልጣኑ የቁጥጥርና የሕግ ማዕቀፎችን በማጠናከር፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና በዲጂታል ሥርዓቶች ውጤታማ አጠቃቀም ረገድ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ገንቢ ውይይት የተደረገበት ነበር።
በጉብኝቱ ወቅት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ በ2018 የበጀት አመት የተከናወኑ ተግባራትን እና የተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶችን ያቀረቡ ሲሆን ፍቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች መጨመራቸው፣ የተለያዩ ቁልፍ መመሪያዎች መፅደቃቸው፣ ረቂቅ መመሪያዎች መዘጋጀታቸው እና በካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳሩ ውስጥ ያለው የቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ መቀጥሉን አንስተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ባለስልጣኑ አዳዲስ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች የፈቃድ አሰጣጥ ላይ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲሁም በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጁ መመሪያዎች በቶሎ ጸድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ብሎም የተጀመሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ ስጥተዋል፡፡