ECMA Gold

ECMA / ኢካገባ

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለ ፕራይም ካፒታል አ.ማ. ፈቃድ ሰጠ።

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለ ፕራይም ካፒታል አ.ማ. የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት ፈቃድ ሰጥቷል። በዚህም ድርጅቱ ከባንክ ቡድን ውጭ በሆነ የኢንቨስትመንት ባንክ ዘርፍ እንዲሠራ ፈቃድ ተሰጥቶቷል። በተጨማሪም ባለስልጣኑ ለ ፕራይም ካፒታል አ.ማ. አራት (4) ተሿሚ እንደራሴዎችም ፈቃድ የሰጠ ሲሆን የዘጠኝ (9) የቦርድ አባላት ሹመትንም አጽድቋል።

የአገልግሎት ሰጪነት ፍቃዱም በዛሬው እለት ማክሰኞ ሚያዚያ 13፣ 2018 ዓ .ም በይፋ የተሰጠ ሲሆን ይህም በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን የተፈቀደላቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ጠቅላላ ቁጥር ወደ አስራ ሰባት (17)፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ባንኮችን ቁጥር ወደ ስድስት (6) ከፍ አድርጎታል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኸልቁ ፈቃዱን በይፋ ለፕራይም ካፒታል አ.ማ. አመራር አስረክበዋል። በፈቃድ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት፣  የኢንቨስትመንት ባንኮች የካፒታል ገበያ ግብይቶችን በማሳለጥ እና ኢንቨስተሮች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ በማድረግ፤ በካፒታል ገበያ ልማት እና በኢንቨስተሮች ጥበቃ ረገድ ያላቸውን ወሳኝ ሚና አፅንዖት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ዋና ዳይሬክተሯ ፈቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች የኮርፖሬት አስተዳደር መርሆችን እንዲያከብሩ፣ የገበያውን ተዓማኒነት እንዲያስጠብቁ፣ ለኢንቨስተሮች ጥቅም ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ እና ለካፒታል ገበያ የቁጥጥር ማዕቀፎች ተገዥነትን እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፕራይም ካፒታል አክሲዮን ማህበርን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን እና የኢንቨስተሮችን ጥበቃ የሚደግፍ ጠንካራ እና አካታች የካፒታል ገበያ ለማጎልበት ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ይገልጻል።