የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከሰፊ የፈቃድ ማመልከቻ ግምገማ ሂደት በኋላ ለሦስት (3) አዳዲስ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች ፍቃድ በመስጠቱ የተሰማውን ደስታ ይገልጻል።
በተጨማሪም ባለስልጣኑ የሦስቱን አዳዲስ አገልግሎት ሰጭዎች አስር (10) ተሿሚ እንደራሴዎችን ፈቃድ ያጸደቀ ሲሆን፣ የ አስራ አምስት (15) ቦርድ አባላት ሹመትንም አጽድቋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ሃና ተኸልቁ ፈቃዱን ሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና መስሪያ ቤት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ለሦስቱ አዳዲስ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች አመራሮች በይፋ ያስረከቡ ሲሆን፣ በባለስልጣኑ ፈቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች ጠቅላላ ቁጥር ከ አስራ ስምንት (18) ወደ ሀያ አንድ (21)፣ ከፍ ሲል፤ የኢንቨስትመንት ባንኮች ቁጥር ወደ ስምንት (8) እና የሰነደ ሙዓለንዋዮች የኢንቨስትመንት አማካሪዎች ቁጥርም ወደ አስራ አንድ (11) ከፍ ብሏል።
አዳዲሶቹ ፈቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች እና የፈቃድ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡
1. ፕራይዝዎርዝ ኢንቨስትመንት ባንክ አ.ማ- በኢንቨስትመንት ባንክ ዘርፍ
2. ብሉፊን ካፒታል አድቫይዘሪ ኃ.የተ.የግ.ማ- በሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት ማማከር ዘርፍ
3. ሉሚና ካፒታል ኃ.የተ.የግ.ማ- በሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት ማማከር ዘርፍ
በፈቃድ አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ላይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ሀና ተኸልቁ በዕለቱ ፈቃድ ለተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ገበያው ከአገልግሎት ሰጭዎች የሚጠብቀውን አገልግሎት በዕውቀት፣ በታማኝነት እና ሁሉንም ኢንቨስተሮች ባማከለ መንገድ አገልግሎታቸውን መስጠት እንዳለባቸው እና በማንኛውም ጊዜ ለህዝብ ጥቅም በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።