ECMA / ኢካገባ

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ጉባዔ በመገኘት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሄደ

MAS00759 1

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች ጉባኤ ላይ በመገኘት ከተቋቋመ ጀምሮ ስላከናወናቸው ተግባራት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በባህርዳር ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሂዷል ፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሩ የካፒታል ገበያ እና የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳር፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት እና የገበያ መሰረተ ልማቶች፣ ዳኞች እና እና ሌሎች የፍትህ ተቋማት በካፒታል ገበያ ውስጥ ያላቸ ሚና በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች እና ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን በመላ አገሪቱ የሚገኙ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና በገበያው እንዲሳተፉ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዚህ ስልጠና አላማም የህግ ማህበረሰቡን በካፒታል ገበያ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማጠናከር በመላ አገሪቱ በካፒታል ገበያ ተቋማት እና በአማራ ክልል በሚገኙ የፍትህ ተቋማት መካከል ዘላቂ የሆነ ትስስር እና ግንኙነት መፍጠር ነው ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ መርሃ ግብሩ የስልጠናው ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ያነሱበት እና ስለ ካፒታል ገበያ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያስቻለ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ዋና ዳይሬክተሯን ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎችም የደም ልገሳ መርሃ ግብር አካሂደዋል፡፡

MAS00327 1